አማርኛ
ትግርኛ
OROMIFFA
ENGLISH

በእርከን ማረሻ

በሥዕል1 የሚታየው መሳሪያ በእርከን ማረሻ ይባላል፡፡ በእርከን ማረሻ ከባህላዊው ማረሻ የሚለየው በድግሩ ብቻነው፡፡ በመሆኑም በባህላዊው የእንጨት ድግር ምትክ ከብረት የተሰራና ከማረሻው ጫፍ ከፍ ብሎ በሚገኝ ደረጃ ከግራና ከቀኝ የሚገኘውንና ባህላዊው ማረሻ የሚዘለውን መሬት ማረስ የሚችል ነው፡፡ በእርከን የተባለበትም ምክንያት በሁለት ደረጃ የሚያርስ በመሆኑ ነው፡፡ በሁለት ደረጃ ማረስ ከመሀል ጥልቀት ያለው እርሻ ለማከናወንና ከግራና ቀኝ ደግሞ በመለስተኛ ጥልቀት በማረስ አረሙን ለመቀጣጠር የሚያስችል ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የታረሰ መሬት በማሳው ውስጥ ወጣገባ ያለ ቅርፅ ይፈጥራል፡፡ ይህም ስውር አርከን ይባላል፡፡ ስውር እርከን የሚፈጠረው የውሀ ልኩን ተከትሎ ነው፡፡ ምክንያቱም በበእርከን ማረሻ ሲታረስ ምንጊዜም ውሀልኩን ተከትሎ ነው እንጅ እንደባህላዊው ማረሻ በመስቀለኛ ስለማይታረስ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ውሀ ልኩን ተከትሎ የሚፈጠሩት ስውር እርከኖች የጎርፍን ሀይል በማዳከም የዝናብ ውሀ ወደ መሬት እንዲሰርግ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በመስክ በተደረገ ጥናት በእርከን ማረሻ ከማሳ ውጭ በጎርፍ አማካኝነት የሚባክንነ የዝናብ ውሀ እስከ 70 በመቶ እንደሚቀንስ ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም የአፈር መከላትን እስከ 80 በመቶ እንደሚቀንስ በመስክ በተደረገ ምርምር ታይቷል፡፡

.

በእርከን ማረሻ ከባህላዊው ማረሻ የሚለይበት ሌላው መንገድ አፈርን አለመገልበጡ ነው፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት የባህላዊው ማረሻ አፈሩን ድግሩ ጫፍ ድረስ ስለሚያነሳው የመገልበጥ እድሉን ሲጨምር በእርከን ማረሻ ግን የተቆረጠው አፈር ባብዛኘው ተመልሶ በነበረበት ቦታእ ንዲቀመጥ ስለሚያደርግ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በትነት መልክ የሚባክነውን የአፈር እርጥበት (ንሽ) በመቆጠብ የአፈሩ እርጥበት እንዲሻሻል ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ሞቃታማ በሆኑና የዝናብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች በተደረጉ የማወዳደሪያ ጥናቶች መሰረት በአማራ ክልል በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አዳማ ቀበሌ በ2008 ዓም የመኸር ዘመን በስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ ድጋፍበ ተደረገ ምርምር የስንዴ ምርት 70 በመቶ፤ ምስር 96 በመቶ እናጤፍ 30 በመቶ መጨመሩ ሲረጋገጥ በኦሮሚያ ክልል በቦሰት ወረዳ ውልንጭቲ አካባቢ በ2007 ዓም የመኸር ዘመን ሰልፍኸልፕ አፍሪካ በተሰኘ ድርጅት በተደረገ የመስክ ሰርቶ ማሳያ የበቆሎ ምርትን እስከ 100 በመቶ እንደሚጨምር ተጠቃሚ አርሶአደሮች አረጋግጠዋል፡፡

በእርከን ማረሻ በበሬዎች በቀላሉ ይጎተታል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ባህላዊው ማረሻ በእንጨት ድግር አፈሩን ለመቁረጥ የሚታገል ሲሆን በእርከን ማረሻ ግን በስለት ስለሚቆርጠው ነው፡፡ በተጨማሪም ሽቅብና ቁልቁል ማረስን ስለሚያስቀር በበሬዎችና በአርሶአደሮች ላይ የሚፈጠረውን የጉልበት ጫና ይቀንሳል፡፡ በእርከን ማረሻ የእርሻ ድግግሞሽን ይቀንሳል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ባንድ ጊዜ እርሻ አፈሩን ሙሉ በሙሉ በመቁረጥ አረሞችን ስለሚቆጣጠርና እንደባህላዊው ማረሻ በመሀል ያለታረሰ መሬት ስለማይተው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ እንደባህላዊው ማረሻ ብዙ ጉሊሳ በማሳው ውስጥ እንዲፈጠር ስለማያደርግ ደጋግሞ ማረስ አስፈላጊ አይሆንም፡፡ በዚህም ምክንያትለ እርሻ ስራ የሚውለው ጉልበትና ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል፡፡

በእርከን ማረሻ የደን መጨፍጨፍን ይቀንሳል፡፡ የባህላዊውን ድግር ለማዘጋጀት የሚቆረጠውን ዛፍ በማስዳን የደንን መጨፍጨፍ መቀነሱ ሌላው የበእርከን ማረሻ ጥቅም ነው፡፡ በእርከን ማረሻ እርከን በተሰራባቸው ማሳዎች ላይ እርሻን ለማከናወን ያመቻል፡፡ ምክንያቱም ውሀልኩን ተከትሎ ስለሚታረስ የእርሻው አቅጣጫ ከእርከኖቹ ትይዩ ስለሚሆን ነው፡፡ በባህለዊው ማረሻ ሲታረስ ግን በመስቀለኛ ማረስ አስፈላጊ ስለሚሆን በሬ ለማዞ አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ እርከኑ እንዲፈርስም ያደርጋል፡፡

በእርከን ማረሻ ከባህላዊው ማረሻ የሚለየው በድግሩ ብቻ ነው፡፡ ለሥራው አመቺነት የበእርከን ማረሻ ድግሮች የራሳቸው ጥቅርት ያላቸው ቢሆንም አርሶአደሩ የራሱን ጥቅርት መጠቀምም ይችላል፡፡ ባህለዊው የእንጨት ድግር ይወገድና የበእርከን ማረሻ ባለክንፍ የብረት ድግሮች በምትኩ ይገጠማሉ፡፡ ከኋላ በኩል በጥቅርቱ አማካኝነት ከሞፈሩ ጋር የሚታሰር ሲሆን ለጥቅርቱ ማስገቢያ ሁለትአ ማራጮች አሉት፡፡ ከኋላ ያሉት ቀዳዳዎች ላይ ሲገጠም የማረሻው ክንፎች አፈሩ እንዳይገለበጥ የሚያደርጉ ሲሆን ከፊት ያሉት የጥቅርት ማስገቢያ ቀዳዳዎች ላይ ሲገጠም ደግሞ ክንፎቹን ወደላይ ስለሚያነሷቸው በእርሻ ወቅት አፈሩ ይገለበጣል፡፡ የጥቅርት ማስገቢያ ቀዳዳዎች ከተመረጡ በኋላ ባህላዊው ወገል ሁለቱን ብረት ጫፎች በመያዝ ልክ እንደባህላዊው ማረሻ ታስሮ ይረገጣል፡፡ ጥንቃቄ፡በእርከን ማረሻን ከገጠምን በኋላ የሞፈሩን ጫፍ በበሬ ልክ በመያዝ ክንፎቹ ከመሬት በላይ ከ6 እስከ 8 ሳሜ ከፍታ ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ክንፎቹ ወደመሬት በጣም የተጠጉ ከሆነ አፈሩን ሙሉ በሙሉ በመላጨት ስውር እርከን እንዳይፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከበእርከን ማረሻ ዋና አላማ ጋር የሚፃረር በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በእርከን ማረሻ የሚያርሰው ውሀልኩን ብቻ ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ይህም እርሻ ከመጀመሩ በፊት መወሰን ይኖርበታል፡፡ የውሀልኩን አቅጣጫ ለማወቅ የአፈርና ውሀ ጥበቃ እርከኖች ሲሰሩ የምንከተለውን አካሄድ መጠቀም በቂ ነው፡፡ በበእርከን ማረሻ ስናርስ የእርሻ ድግግሞሹን መቀነስ አለብን፡፡ በምን ያህል ይቀነስ የሚለውን ለመወሰን ግን እንደአፈሩና እደአረሙ ሁኔታ አርሶአደሩ እራሱ እንዲወስን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የበርከን ማረሻና የአይባር ታይ ሪጀር ቅንጅት

በርከን ማረሻና የአይባር ታይ ሪጀር በቅንጅት ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚሆነው አፈሩ እንዲገለበጥ ሲፈለግ ወይም ውሀ ለመቀጠር ድርዳሮ ማከናወን ሲፈለግ ነው፡፡ አሰራሩም እንደሚከተለው ነው፡፡ በመጀመሪያ ማሳው በበርከን ማረሻ ይታረሳል፡፡ ቀጥሎ ድርዳሮው በሚፈለግበት ወይም አፈሩ መገልበጡ በሚፈለግበት ወቅት አይባር ታይሪጀር ይገጠማል፡፡ አይባር ታይሪጀሩ ቀድሞ በርከን ማረሻው በሄደበት መስመር እንዲሄድ ይደረጋል፡፡ ሆኖም አይባር ታይ ሪጀር ባንድ ጊዜ የሚሸፍነው መሬት ሰፊ ስለሆነ ሲመለስ በርከን ማረሻው የሄደበትን አንድ ፈር (መስመር) በመዝለል በሁለተኛው መሄድ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የእርሻ ሥራውን ፈጠን ከማድረግ በተጨማሪ በርከን ማረሻው የፈጠራቸው ስውር እርከኖች እንዳይፈርሱ ማድረግ ይቻላል፡፡